ወንጌል እና ወንጌልን እንዴት ማካፈል እንደሚቻል
የእግዚአብሔርን ታሪክ ለማካፈል ብዙ መንገዶች አሉ። በጣም የተሻለው መንገድ እርስዎ በሚያካፍሉት ሰው፣ ስለ ዓለም ባለው እይታ እና በሕይወት ልምዶቹ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። እግዚአብሔር ለማካፈል ፈቃደኛ የሆኑ ልቦችን በመጠቀም ለመስማት ፈቃደኛ በሆኑ ልቦች ላይ ይሠራል። የእግዚአብሔርን ታሪክ የምናካፍልበት አንዱ መንገድ ከእግዚአብሔር ፍጥረት ጀምሮ እስከ ዚህ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ያለውን ፍርዱን በማስረዳት ነው።
የእግዚአብሔር ታሪክ፡ ከፍጥረት እስከ ፍርድ አቀራረብ
በመጀመሪያ እግዚአብሔር መላውን ዓለምና በውስጡ ያለውን ሁሉ ፈጠረ።
የመጀመሪያውን ወንድ እና የመጀመሪያዋን ሴት ፈጠረ። በሚያምር አትክልት ስፍራ ውስጥም አኖራቸው። የቤተሰቡ ክፍል አደረጋቸው እና ከእነርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው።
ለዘላለም እንዲኖሩ ፈጠራቸው። ሞት የሚባል ነገር አልነበረም። በዚህ ፍጹም ስፍራ እንኳን ሰው በእግዚአብሔር ላይ አመፀ እና ኃጢአትን እና ሥቃይን ወደ ዓለም አመጣ። እግዚአብሔርም ሰውን ከአትክልት ስፍራው አባረረው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ግንኙነት ተሰበረ። አሁን ሰው ሞትን መጋፈጥ ነበረበት። በብዙ መቶዎች ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር መልእክተኞችን ወደ ዓለም ይልክ ነበር። እነርሱም ሰውን ስለ ኃጢአቱ ያስታውሱት ነበር፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ታማኝነት እና አዳኝን ወደ ዓለም ለመላክ ስላደረገው ተስፋም ይነግሩት ነበር።
አዳኙ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን የቀረበ ግንኙነት ይመልሳል። አዳኙ ሰውን ከሞት ያድናል። አዳኙ የዘላለም ሕይወትን ይሰጣል እና ከሰው ጋር ለዘላለም ይኖራል። እግዚአብሔር እጅግ ስለሚወደን ጊዜው በደረሰ ጊዜ ልጁን ወደ ዓለም ላከው ያ አዳኝ እንዲሆን።
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር። በድንግል ወደ ዓለም ተወለደ። ፍጹም ሕይወት ኖረ። ፈጽሞ ኃጢአት አልሠራም። ኢየሱስ ሰዎችን ስለ እግዚአብሔር አስተማረ። ታላቅ ኃይሉን የሚያሳዩ ብዙ ተአምራትን አደረገ። ብዙ አጋንንትን አወጣ። ብዙ ሰዎችን ፈወሰ። ዕውራንን እንዲያዩ አደረገ። ደንቆሮዎችን እንዲሰሙ አደረገ። አንካሶችን እንዲራመዱ አደረገ። ኢየሱስ ሙታንን እንኳን ከሞት አስነሳ። ብዙ ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ምክንያት ስጋት ተሰማቸው እና ቀኑበት።
እርሱን ለመግደል ፈለጉ። ፈጽሞ ኃጢአት ስላልሠራ ኢየሱስ መሞት አያስፈልገውም ነበር።
ነገር ግን ለሁላችን መስዋዕት ሆኖ መሞትን መረጠ። የእርሱ ሕመም የበዛበት ሞት የሰው ልጆችን ኃጢአት ሸፈነ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቃብር ተቀበረ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ያቀረበውን መስዋዕት አይቶ ተቀበለው። እግዚአብሔር ይህን መቀበሉን በሦስተኛው ቀን ኢየሱስን ከሞት በማስነሣት አሳየ።
እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ ስለ ኃጢአታችን የተደረገውን የኢየሱስን መስዋዕት ብናምንና ብንቀበል -- ከኃጢአታችን ብንመለስ እና ኢየሱስን ብንከተል፣ እግዚአብሔር ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል እና ወደ ቤተሰቡ እንደገና ይቀበለናል።
እግዚአብሔር ኢየሱስን እንድንከተል እንዲያስችለን በውስጣችን እንዲኖር መንፈስ ቅዱስን ይልካል። ይህ የተመለሰ ግንኙነት ምልክትና ማረጋገጫ እንዲሆን በውኃ ጥምቀት እንጠመቃለን።
የሞት ምልክት እንደሆነ በውኃ ውስጥ እንቀበራለን። የአዲስ ሕይወት ምልክት እንደሆነ ኢየሱስን ለመከተል ከውኃው እንነሣለን።
ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ 40 ቀናት በምድር ላይ ቆየ።
ኢየሱስ ተከታዮቹን በየቦታው ሄደው ስለ ማዳኑ የሆነውን ምሥራች ለዓለም ሁሉ ሰዎች እንዲነግሩ አስተማራቸው። ኢየሱስም፣ - ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲታዘዙ አስተምሯቸው። እኔም እስከዚህ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ አለ።
ከዚያም ኢየሱስ በዓይናቸው ፊት ወደ ሰማይ ተወሰደ። አንድ ቀን ኢየሱስ እንደሄደበት ሁኔታ እንደገና ይመጣል። ያልወደዱትንና ያልታዘዙትን ለዘላለም ይቀጣል። የወደዱትንና የታዘዙትን ግን ለዘላለም ይቀበላል እና ይሸልማል። ከእርሱ ጋር ለዘላለም በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር እንኖራለን።
እኔ ስለ ኃጢአቴ ኢየሱስ ያደረገውን መስዋዕት አምኜ ተቀብያለሁ። እርሱ አንጽቶኛል እና እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ክፍል መልሶኛል። እርሱ ይወደኛል፣ እኔም እወደዋለሁ እና በመንግሥቱ ውስጥ ለዘላለም ከእርሱ ጋር እኖራለሁ። እግዚአብሔር እርስዎንም ይወዳል እና ይህን ስጦታ እንዲቀበሉ ይፈልጋል። ይህን አሁን ማድረግ ይፈልጋሉ?
ይህን የወንጌል አቀራረብ ታሪኩን በምቾት መንገር እስክትችሉ ድረስ በራሳችሁ ተለማመዱ።
እራሳችሁን ጠይቁ
- ይህን ታሪክ በቃል ማካፈል ትችላላችሁ? ሁሉም ሰው የወንጌልን ታሪክ በልምምድ የበለጠ ይሻሻላል። አሁን ቆማችሁ 3 ጊዜ ተለማመዱ።
- ከዚህ ታሪክ ስለ ሰው ልጅ ምን ትማራላችሁ?
- ስለ እግዚአብሔርስ ምን ትማራላችሁ?
- የእግዚአብሔርን ታሪክ እንደዚህ ባለ ታሪክ በመንገር ማካፈል ቀላል ወይስ ከባድ ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
የZúme ስልጠናን ዛሬ ይጀምሩ
ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው፣ እናም በማንኛውም ጊዜ መጀመር ይችላሉ—የትም ቢሆኑ በራስዎ ፍጥነት ይሂዱ።
በነጻ ይመዝገቡ